የግንቦት 20 ሃያ ሰባተኛ ዓመት በዓል በጄኔቫ በድምቀት ተከበረ !

27ኛው የግንቦት 20 በዓል “የላቀ ብሔራዊ መግባባትና ዲሞክራሲያዊ አንድነት ለላቀ አገራዊ ስኬት” በሚል መሪ ቃል በጄኔቫ በሚስዮኑ መኖሪያ ግቢ ውስጥ ተከበረ፡፡

በዓሉ ተቀማጭነታቸው ጄኔቭ የሆኑ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች፣ የተ.መ.ድ. እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ በስዊዘርላንድ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡

ክቡር አምባሳደር ነጋሽ ክብረት 27ኛው የግንቦት 20 ክብረ በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ግንቦት 20 በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባታ የህዝቦች መብት መከበር፣ ለኢኮኖሚያችን ዕድገት መፋጠን እና ለህዳሴያችን ጉዞ መሰረት የተጣለበት ቀን ነች ብለዋል፡፡

ብዙሃነት የተቀበለና ያከበረ የፌዴራል ስርዓት የተገነባበት ዕለት መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር፣ በራስ ቋንቋ የመማር፣ ባህልና ታሪክ የማሳደግ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የተጎናጸፍንበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት ድህነት ላይ በተካሄደው ዘመቻ በአገራችን ብሩህ ተስፋ እንዲለመልም ማድረግ የተቻለበት፣ ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የቻልንበት፣ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለማጠናከር፣ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት የተደረገበት፣ የአሸናፊነት ልቦና የተላበስንበት መሆኑን አምባሳደሩ አክለው ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገራችን ሰላም ላይ አደጋ ተጋርጦ የነበረ ቢሆንም የተፈጠሩት ችግሮች እንደአገር የተመዘገበውን ድልና ውጤት አያደበዝዘውም ብለዋል፡፡ ከነበርንበት ሀገራዊ ቀውስ ተላቀን ሰላምና መረጋጋት በአስተማማኝ መሠረት እንዲቀጥል መንግስት እና ህዝብ አንድ ላይ ሆነን የአዲስ ምዕራፍ ጉዞ በጀመርንበት ወቅት የምናከብረው በዓል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በህዝባችን አርቆ አሳቢነት ትግል በተደረገው የአመራር ሽግሽግ ከወዲሁ ለውጥ መታየቱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል፣ በአገራችን ሰላም እንዲወርድ፣ ይቅርታ የማድረግ፣ እስረኞችን የመፍታትና ክሶችን ማቋረጥ፣ ሙስናን እና ኮንተሮባንድ የመታገሉ ጥረት ሊጠቀስ ይችላል ብለዋል፡፡

ግንቦት 20 ስናከብር የመልካምነት፣ የፍቅረ፣ የአብሮነት እና የሰላም እሴቶቻችን የዘመናዊነታችንና የስልጣኔያችን አይነተኛ ማሳያ ማድረግና ለተሻለች አገርና ብልጽግና ስኬቶቻችንን ለማስፋት፣ ድክመቶቻችንን ለማረም ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ መረባረብ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም በዓሉ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ተጨማሪ እድገትና ብልጽግና፣ በኢትዮጵያና ስዊዘርላንድ የትብብር ግንኙነት መጠናከር፣ የተ.መ.ድ. መልካም ግንኙነት ቀጣይነት ተመኝተዋል