የኢህአዴግ ሊቀመንበር ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ነበረ:- የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት

የኢህአዴግ ሊቀመንበር ምርጫ ዴሞክራሲያዊና የግንባሩን አንድነት በሚያጠናክር መልኩ መከናወኑን የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገለጹ።
ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሲካሄዱ የነበሩትን የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባዎች አስመልክተው የድርጅቱ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ሽፈራው በስብሰባዎቹ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ባለፈው ታህሣስ ወር በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ያደረጉት ግምገማና አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታ ተገምገሟል ብለዋል።
በግምገማዎቹ ድክመትና ጥንካሬ የተለየበትና ቀጣይ አገራዊ ሁኔታ ለማስተካከል አቅጣጫ የተቀመጠበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ ስብሰባ ድርጅቱ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን የግንባሩ የሊቀመንበርነት መልቀቂያን መቀበሉን ተከትሎ ተተኪ የግንባሩ ሊቀመንበር በመምረጥ ተጠናቋል ብለዋል።
የምርጫ ሂደቱ በጥልቅ ግምገማና ዴሞክራሲያዊ ሂደት የተከናወነ ነው ያሉት አቶ ሽፈራው፤ ምርጫው በቀጣይ የግንባሩን አንድነት የሚያጠናከር እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የምርጫ ሂደቱ በሚስጢራዊ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት መካሄዱን የገለጹት አቶ ሽፈራው በመድረኩ ከቀረቡ ሦሰት ዕጩዎች መካከል ዶክተር አብይ አህመድ የግንባሩ ሊቀ መንበር ሆነው መመረጣቸውን ተናግረዋል።