በጄኔቫ የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤት የኢትዮጵያዊያን የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር በዓል ተከበረ

       

በጄኔቫ የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው አዲስ የተሸሙት ክቡር አምባሳደር ዘነበ ከበደ የኢትዮጵያዊያን የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመደመር የትውውቅ በዓል ላይ በመገኘት መልዕክት አስተላፈዋል፡፡
የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር በዓል ላይ ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ዘነበ ከበደ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያን የጋራ ወደ ሆነው ቤታቸው በመምጣታቸው ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በስዊዘርላንድና ሚሲዮኑ በተወከለባቸው ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸውን ለማገልገል ዕድል በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በፍቅርና በመተሳሰብ በቤተሰባዊ የአንድነት ስሜት መሰባሰብ በመቻላቸው ኩራት ሊሰማቸው ይገባል ብለዋል።
ክቡር አምባሳደር ዘነበ የኢትዮጵያዊያን የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር በዓል በአንድ በኩል በዚህ የአንድ ዓመት የለውጥ ሂደት ያገኘናቸውን ውጤቶች እያጣጣምን በተጨማሪ ደግሞ መድረኩን ተጠቅመን በመተዋወቅ ለወደፊቱ በጋራ ጥረታችን የበለጠ አጠናክረን ለማስቀጠል ቃል የምንገባበት ቀን እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ስናገለግላቸው ብቻ ሳይሆን በአካል ስናገኛቸውም ውስጣዊ ደስታ፣ ክብርና ኩራት ይሰማናል ያሉት ክቡር አምባሳደሩ ሚሲዮናችን ያለምንም የፖለቲካ አመለካከት፣ የብሄር፣ የእምነት፣ ወዘተ ልዩነት በፍጹም አገራዊ የዜግነት ስሜትና በፍቅር በራችንና ልባችንን ከፍተን ልናገለግላችሁ ዝግጁና ደስተኞች መሆናችንን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ብለዋል።
ሀገራችን በአዲስ የለውጥ ጎዳና መጓዝ ከጀመርች አንድ ዓመት ማሳለፋን አምባሳደሩ ጠቅሰው፣ በዚህ የለውጥ ሂደት በርካታ ድሎች የተመዘገቡ መሆናቸውን፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አባላትም ሲደሰቱ፣ ሲደነቁ ሲመሰክሩ እያየንና እየሰማን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ጉዞ ላይ እንገኛለን ያሉት ክቡር አምባሳደር በትጋት፣ በጽናት፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመከባበር፣ በመተባበር፣ ሀገራዊ አንድነትና አርቆ አሳቢነት መንፈስ የልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችንን መጻዒ እድል አስበን የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ በጽናትና በጥንካሬ ልናስቀጥል እንደሚገባ ክቡር አምባሳደር ገልጸዋል፡፡
ሥር ሰደው በቆዩት አላስፈላጊ አስተሳሰቦች፣ በጥቅም ላይ በተመሰረቱ ሕገወጥና ከፋፋይ ትስስሮች፣ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንንና በጨዋነት ተሳስቦ አብሮ የመኖር እሴትና ባህላችንን በሚሸረሽሩ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች የተነሳ እያጋጠሙን ያሉ ችግሮችና እየደረሱ ያሉ ጉዳቶች በአንድ በኩል የሚሳዝኑንና የሚያሳስቡን ሲሆን በሌላ በኩል የበለጠ ተቀራርበንና ተባብረን፣ በሰለጠነና በተረጋጋ መንፈስ ተመካክረን እንድንመክትና የተጀመረው አገራዊ ለውጥ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል በእልህ፣ በቁጭትና ብስለት በተሞላበት ሁኔታ እንድንሰራ የሚያበረታታን ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዓብይ አህመድ « ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገባ » በማለት በውጭ ለምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን መልዕክት ካስተላለፉበት እለት ጀምሮ በናንተና በሚሲዮናችሁ መካከል የነበረውን ግንብ በማፍረስ ለጋራ ሀገራችን በጋራ መቆም ለመጀመራችን የእናንተ የወገኖቼ አዎንታዊ ምላሽና ሚና በጣም ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ አጋጣሚ ልባዊ ምስጋና ልንገልጽላችሁ እንወዳለን ብለዋል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትራችን እንዳሉት ‘አንድ መሆን ማለት አንድ ዓይነትነት ማለት አይደለም፡፡ ሁላችንም እንደመልካችን በአመለካከት፣ በእምነት፣ በእውቀት እንዲሁም በቁሳዊ ሀብት ልንለያይ እንችላለን። ነገር ግን በሰውነታችንና በኢትዮጵያዊነታችን ማንም ከማንም አይበልጥም፣ ማንም ከማንም አያንስም። እናም በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊ ዜግነታችን እንዲከበር፣ እናት ሀገራችን ታፍራና ተከብራ፣ አድጋና ለምታ፣ ሁሉም ሊኖርባት የሚመኛት እንድትሆን፣ ሕዝቦቿ ከችግር ተላቀው፣ በኢትዮጵዊነታቸው ኮርተው እንዲኖሩ አንድነታችን ላይ አጥብቀን ልናተኩር ልንሰራ እንደሚገባ ክቡር አምባሳደር ዘነበ ገልጸዋል።
በሀገራችን ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና እንዲመጣ መከተል በሚገባን መንገድ ላይ አንዳችን ከሌላችን በሀሳብ ልንለያይ እንችላለን ያሉት ክቡር አምባሳደሩ፣ ይህ ልዩነት ጤናማና ተፈጥአዊ ነው፣ እንዲህ ዓይነቱ ልዩነት ከሌለ ለውጥና እድገት ሊኖር አይችልምና በሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ መንገድ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተስማማንባቸው ጉዳዮች ተባብረን መስራት፣ ባልተስማማንባቸው ጉዳዮች ሳንጣላና ሳንጠላላ ተከባብረን መኖር እንደሚያስፈልገን ገልጸዋል።
የሀገራችን እድገትና ልማት የተፋጠነ እንዲሆን በግልም ሆና በቡድን ሁላችሁም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያ እያደረጋችሁ ያላችሁት አስተዋጽዎ፣ በተለይ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ለተጎዱ ወገኖቻችን እርዳታና ድጋፍ በማድረግ፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ በመሰማራት፣ የእውቀት ሽግግር በማድረግና በህጋዊ መንገድ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ቤት በመላክ እያበረከታችሁ የምትገኙት አስተዋጽኦ እጅግ የሚያኮራና የሚያስመሰግን ተግባር ነው ያሉት ክቡር አምባሳደሩ፣ ለወደፊቱም በየግላችሁም ሆነ በጋራ በሀገራችሁ ልማትና እድገት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆኑ ሁኔታዎችን ለማመቻቸትና ለመደገፍ፣ ከሚሲዮኑ ድጋፍና አገልግሎት ስትፈልጉ አቅማችንና ሁኔታው በፈቀደ መጠን በፍቅርና በደስታ ልናገለግላችሁ፣ ሕግና ስርዓትን ተከትለን መብቶቻችሁንና ጥቅሞቻችሁን ለማስጠበቅ ዝግጁ በመሆናችን ተቀራርበን፣ ተመካክረንና ተቀናጅተን በፍጹም አገራዊ የአንድነት ስሜት እንድንሰራ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋ