በጀርመን ፍራንክፈርት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር የሚያደርጉት ውይይት

የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ አቀባበልና ንግግር በፍራንክፉርት

«አንድ ሆነን እንነሳ፣ ነግንም እንገንባ» በሚል መርህ ቃል ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ዛሬ ቀትር ላይ በፍራንክፉርት «ኮሜርስ ባንክ አሬና» በተባለዉ ስቴዲየም ተገኝተዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትዉልድ ኢትዮጵያዊያን ጠቅላይ ሚንስትሩን በጭብጨባና በደስታ ተቀብለዋቸዋል። ዝግጅቱም በሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች ምርቃት ተጀምረዋል። የፍራንክፉርት ከተማ ማርሽ ባንድም በባህላዊ ሙዚቃ መሳርያቸዉ ዝግጅቱን አድምቀዋል። በመቀጠልም ታዳጊ ወጣቶች በአፋን ኦሮሞና በአማርኛ ለጠቅላይ ሚንስትሩና ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መዝሙር አቅርበዋል። በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ኩማ ደመቅሳ በፍርንክፉርት የኢትዮጵያ ቆንፁላ ዋና ስራ አስካያጅ አቶ ምህረተአብ ሙሉጌታና የፍራንክፉርት ምክትል ከንቲባ ባደረጉት ንግግርም በኢትዮጵያ ዉስጥ እየታየ ስላለዉ ለዉጥ አድናቆታቸዉን ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በጀርመንኛ ቋንቋ ሰላምታቸዉን ካቀረቡ በዋላ ንግግራቸዉን አድርገዋል። "አሁን ያላየነውን የምናይበት፤ ያልሞከርነውን የምንሞክርበት ጊዜ ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ "ኢትዮጵያ ማንም ተነስቶ በወደደው ልክ እና ፍላጎት እንደ ቂጣ የሚጠፈጥፋት ሳትሆን ታላቅ ህዝብ የመሰረታት ታላቅ ሀገር ናት" ንግግር በታዳሚያኑ የተወደደ ይመስላል። በይደገም ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን አባባላቸውን በንግግራቸው ደግመውታል። "ሀገሬ አንቀላፍታ ይሆናል እንጂ አልሞተችም" ሲሉም በከፍተኛ ድምፅ የታጀበ ድጋፍ ተለግሷቸዋል። በአዉሮጳ የሚኖሩት ኢትዮጵያዉያን ከዉጭ ሆኖ ከመተቸት ባለፈ በኢኮኖሚዉም ሆነ በፖለቲካዉ እንዲሳተፉ ጋብዘዋል።ማሳሰቢያ፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ ንግግርን ከ1:07:48 ጀምሮ ይመልከቱ

Posted by DW Amharic on Wednesday, 31 October 2018